fbpx
Connect with us

የአንጀት ብግነት የቤት ዉስጥ ዘላቂ መፍትሄዎች

Social Mediaፀ

ህክምና

የአንጀት ብግነት የቤት ዉስጥ ዘላቂ መፍትሄዎች

የአንጀት ብግነት ህመም ምንድነዉ?
የአንጀት ብግነት ወይም (Irritable Bowel Syndrome) የምንለዉ ህመም ለረጅም ጊዜያት ወይም አመታት ሊቆይ የሚችል አልፎ አልፎ የሚከሰት የሆድ ህመም ነዉ። ይሄም ህመም የሚከሰተዉ አንጀታችን ላይ ምንም የሚታይ እንከን ወይም ቁስል ሳይኖር ቢሆንም በታማሚዎች ላይ በሚታዩት የተለያዩ ምልክቶች የተነሳ ጤናን በማቃወስ ኑሮን ከባድ ያደርገዋል።

በዚህ ህመም የሚቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉም ቢሆኑም በአብዛኛዉ ወጣቶች ላይ የሚታይ ሲሆን ሴቶች በአመዛኙ የችግሩ ሰለባ ናቸዉ። በተደረጉት ጥናቶች እስከ 33 በመቶ የሚሆኑ እድሜአቸዉ ከ አስራዎቹ እስከ አርባ የሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ይታያል።
የህመሙ ምልክቶች በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች የመደባሉ፡-
1ኛ. ከወትሮዉ የተለየ የአንጀት ባህሪይ
2ኛ. ከፍተኛ የሆነ በየጊዜዉ የሚለዋወጥ ባሪይ ያለዉ የሆድ ቁርጠት እና የሆድ ጩኸት
3ኛ. የሆድ መነፋት ወይም መለጠጥ ስሜት ናቸዉ።

1ኛ. ከወትሮዉ የተለየ የአንጀት ባህሪይ፡-
የሚቀያየር የሆድ ድርቀት ወይም ማስቀመጥ፣ በሰገራ ጊዜ ህመም መሰማት ወይም በሚሰጡ መድሃኒቶች የማይሻል የሆድ ድርቀት፣ ቶሎ ቶሎ ሰገራ የመምጣት ስሜት መሰማት፣ ትንሽም ቢሆን ምግብ ከተበላ በኋላ የሰገራ መወጠር ስሜት መሰማት ናቸዉ።
2ኛ. ከፍተኛ የሆነ በየጊዜዉ የሚለዋወጥ ባህሪይ ያለዉ የሆድ ቁርጠት እና የሆድ ጩኸት፡- ይሄም የሁድ ቁርጠት ብዙ ጊዜ የሚከሰተዉ ከእምብርት በታች ሲሆን አብዛኛዉን ጊዜ በስተግራ በኩል ነዉ። ህመሙ ምግብ ከተበላበት ጥቂት ጊዜ በኋላ ወዲያዉ ሊጀምር ይችላል። ህመሙ ወደ ሽንት ቤት ተኪዶ ፈስ ከወጣ በኋላ የመቀነስ ባህሪ በብዛት ይታይበታል። የሆድ ጩኸቱ ደግሞ ከፍተኛ የሆነና ሌሎች አጠገብ ላሉ ሰዎች የሚሰማ በመሆኑ ታማሚዎቹን ብዙ ጊዜ የሚያሸማቅቅ ነዉ።
3ኛ. የሆድ መነፋት ወይም መለጠጥ ስሜት፡- ከዚህ የተነሳ በግራ በኩል ልብ አከባቢ ላይ ካለዉ አንጀት መወጠር የተነሳ የልብ ህመም ይመስል ህመም ሊሰማ ይችላል።
ከላይ ከተጠቀሱት ከሶስቱ ጋር በተጨማሪ ወይም ለብቻ ከሚከሰቱት ሌሎች ምልክቶች መካከል፤ ከሰገራ ጋር የሚወጣ ዝልግልግ ፈሳሽ፣ የደረት ማቃጠል እና የእህል ያለመፈጨት፣ ማቅለሽለሽ ወይም ማስመለስ፣ ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት እና ያለመታገስ፣ ከፔሬድ በፊት የሚከሰት ከባድ ህመም፣ የወሲብ ፍላጎት መቀነስ ወይም በወሲብ ጊዜ ህመም መሰማት እና የመገጣጠሚያ ህመም ይገኙበታል።

ህመሙ ሳይታወቅ ወይም መፍትሄ ሳይገኝለት የሚቆይበት ምክንያት ምንድነዉ?
ብዙ ጊዜ ይህ ህመም በአብዛኛዉ ይከሰት የነበረዉ በምዕራቡ አለም ሲሆን፣ አሁን ግን የኛም አመጋገብ ስርዓት በአብዛኛዉ ወደነሱ እያደላ በመምጣቱ፣ ማለትም ለምሳሌ ፕሮሰስ የተደረጉ ምግቦችን በብዛት መጠቀማችን እና በቂ ንጹህ ዉሃ ያለመዉሰዳችን ይሄንን ህመም በህብረተሰባችንን እየተስፋፋ እንዲሄድ እያደረገዉ ነዉ። አንድ ሰዉ ሆዴን አመመኝ ብሎ ወደ ክሊኒክ ሄዶ ቢያማክር በመጀመሪያ ደረጃ በሚደረጉለት ምርመራዎች ምንም ስለማይገኝ (ማለትም በደም፣ ሰገራ እና ሽንት ምርመራዎች)፣ በቃ ችግርህ ጨጓራ ነዉ ይባል እና የጨጓራ መድሃኒት በተደጋጋሚ ቢወስድም ምንም መፍትሄ ሳያገኝ ይቀራል። ህመሙም የራሱ የሆነ መመርመሪያ መንገድ የሌለዉ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ታማሚዎች ህመሙ እንዳለባቸዉ የሚነገራቸዉ የአንጀት ስፔሺያሊስት ጋር ሲደርሱ ሌሎች ህመሞች በተለያዩ ምርመራዎች ያለመኖራቸዉ ከተረጋገጠ በኋላ ሲሆን ይህ ደግሞ በህመሙ ረጅም ጊዜ እንዲሰቃዩ ያደርጋቸዋል። ምርመራ ከሚደረግባቸዉ ሌሎች ህመሞች መካከል፡- የታይሮይድ ወይም የፓራታይሮይድ ሆርሞን ችግሮች፣ ጂያርዲያ እና ሌሎች መሰል የአንጀት ተዉሳኮች ሰገራ ምርመራ፣ የደም ሴል ቁጥር ምርመራ ይገኙበታል።
ለህመሙ ከሚደረጉ የዘመናዊ መድሃኒት ህክምናዎች መካከል፡- ለሆድ ቁርጠት ማስታገሻ የሚሆኑ፣ ለተቅማጥ የሚሰጡ፣ ለህመም ማስታገሻ የሚሆኑ፣ የሆድ ድርቀት መከላከያ የሚሆኑ፣ እንደታካሚዉ ሁኔታ በሃኪሙ ሊታዘዙ ይችላሉ። በህክምና የሚሰጡ መድሃኒቶቹ አብዛኞቹ የሚሰጡት መፍትሄ እምብዛም መሆኑ እና ጊዜያዊ መፍትሄ ብቻ ስለሆነ የሚገኝባቸዉ በቤት ዉስጥ የሚደረጉ መፍትሄዎች ላይ በማትኮር እና ራስን ከመጨናነቅ በመጠበቅ የተሻለ ህይወት መኖር ይቻላል።

የአንጀት ብግነት የቤት ዉስጥ ህክምና መፍትሄዎች
በመድሃኒቶቹ የሚገኘዉ መፍትሄ ዘላቂ ባለመሆኑ በተቻለ መጠን ከዚህ በታች የተጠቀሱትን የተወሰኑ አመጋገብ እና የኑሮ ዘይቤ ላይ ለዉጥ በማድረግ የተሻለ ህይወት መኖር ይቻላል።
1ኛ. በተቻለ መጠን ፕሮሰስ ከተደረጉ ምግቦች መሸሽ (የታሸጉ ወይም የፋብሪካ)። ፕሮሰስ የተደረጉ ምግቦች ሲባል፣ ለምሳሌ ማንኛዉም አይነት የፋብሪካ ስንዴ ዱቄት እና ምርቶቹን በተቻለ መጠን መቀነስ ወይም ደግሞ አቁሞ ለዉጡን ማየት። በዚህ ምትክም የገብስ ወይም ደግሞ ቤት ዉስጥ ተፈጭቶ የተጋገረዉን የስንዴ ዳቦ መጠቀም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለምግብ ማብሰያነት እና ማጣፈጫነት የምንጠቀማቸዉ ነገሮችም ላይ ትኩረት ብናደርግ መልካም ነዉ። ለምሳሌ በተቻለ መጠን ማንኛዉንም በኖርማል ሙቀት የማይቀልጡ ዘይቶችን ማስወገድ ቢቻል ወይም ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ አቁሞ ለዉጡን ማየት።
2ኛ. የችግሩ መንስኤዎች መካከል ዋነኛዉ የሆነዉ በምግባችን ዉስጥ ያለዉ የፋይበር መጠን መቀነስ ስለሆነ ቢቻል ባገኙት አጋጣሚ በፋይበር የበለጸጉ ምግቦችን ማዘዉተር። በፋይበር ከበለጸጉት ምግቦች መካከል፡- የጓሮ አትክልቶችን እና ፍራፍሬዎችን ማለትም፡- እንደ ጎመን፣ ሳላጣ፣ አፕል፣ እና ከአዘርት ደግሞ በቆሎ፣ ገብስ፣ ምስር፣ አደንጓሬ መመገብ።
3ኛ. ብዙ ጊዜ ሰዎችን ለህመም ከሚዳርጋቸዉ ዋነኛ ስሀተት መካከል አንዱ በቂ ዉሃ ያለመጠጣት ሲሆን። በቂ የሆነ ዉሃ መጠጣት የሚባለዉ ራሱን ችሎ ከምግብ ዉጪ የሚወሰድ ዉሃ ነዉ። በቂ ዉሃ በቀን ዉስጥ መጠጣታችንን የምንለካዉ ደግሞ በምንሸናዉ የዉኃ ሽንት መጠን ነዉ። ይሄም ማለት ትንሽ ትንሽ ዉሃ ብዙ ጊዜ በቀን ዉስጥ ከምግብ ሰዓት ዉጪ መጠጣት እና ቢያንስ በቀን ከሁለት እስከ ሶስት ጊዜ ሽንት መሽናትዎን በማረጋገጥ ነዉ። ቢቻል ሌሊት ከእንቅልፍ ሲነቁ እና ማታ ሊተኙ ሲሉ የሚችሉትን ያህል ዉሃ መጠጣት የአንጀት ብግነትን ይቀንሳል።
4ኛ. በተቻለ መጠን የአልኮል፣ የቡና እና ጫት መጠን መቀነስ ወይም ብብዛት የሚወስዱ ከሆነ ማቆም። ምክንያቱም ሶስቱም ከሰዉነት በሽንት ዉሃ ስለሚያስወግዱ መጠኑን መቀነስ ወይም አስገዳጅ ከሆነ ከመጠቀምዎ በፊት ዉሃ መጠጣት ያስፈልጋል።
5ኛ. ለህመሙ መንስኤ ከሚባሉት አንዱ የሆነዉ መጨናነቅ በመሆኑ፣ በተቻለ መጠን ራስን ከሚያጨናንቁ ሁኔታዎች ማራቅ ወይም እርዳታ ከስነልቦና ባለሙያ ማግኘት እና ራስን ማረጋጋት፤ ይሄም ደግሞ ከፍተኛ ዉጤት ያስገኛል።
ለጥያቄ ወይም ለማማከር በፌስቡክ ወይም ቴሌግራም ያግኙኝ።
አመሰግናለሁ።
ዶክተር ተመስገን እንዳለዉ

MD, Lecturer, UX & UI Developer, Consultant SMM, and Blogger.

3 Comments

More in ህክምና

To Top