fbpx
Connect with us

13 የብልጽግና አስተሳሰብ መርሆች

think and grow rich
pixabay

ካነበብኳቸዉ

13 የብልጽግና አስተሳሰብ መርሆች

በስኬታማ ሰዎች መንደር እጅግ የሚታወቀዉና ለረጅም ጊዜያት ከፍተኛ ሺያጭ የነበረዉና ከምንግዜም አስር ምርጥ መጽሃፎች መካከል አንዱ የሆነዉ የ ናፖሊዮን ሂል Think and Grow Rich የሚባለዉ መጽሃፍ ነዉ። ይሄም መጽሃፍ ማንኛዉም በህይወቱ ትርጉም ለሚፈልግ ሰዉ ስንቅም ተደርጎ በብዙዎች ዘንድ ይወሰዳል። እኔም ይሄንን መጽሃፍ ደጋግሜ ካጣጣምኳቸዉ መጽሃፎች አንዱ ሲሆን የሚያትታቸዉን ቁምነገሮች እምብዛም የንባብ ልምድ ለሌላቸዉና ጊዜ ለሚያጥራቸዉ ሰዎች በማሳጠር 13 የብልጽግና አስተሳሰብ መርሆች በማለት አቅርቤላችኋለሁ። መልካም ንባብ።
ይሄ ከ 80 ሚሊየን በላይ ኮፒዎች በመሸጥ የሚንጊዜም በብዛት የተሸጡ መጽኃፎች ዝርዝር ዉስጥ የተካተተ መጽሃፍ የተጻፈዉ ናፖሊዮን ሂል በተባለ ጸሃፊ ሲሆን እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ 1937 አንድሪዉ ካርኒጌ በተባለ አንድ አሜሪካዊ ባለሃብት አነሳሽነት ነበር። መጽሃፉም የተጻፈዉ በአሜሪካ የሚገኙ 500 ባለ ሃብቶችን ቃለመጠይቅ በማድረግ ነዉ። ጸሃፊዉም ከ 500 ባለ ሃብቶች ያገኘዉን መረጃ በማቀናጀት ThinK and Grow Rich የተባለዉን መጽኃፍ አሳተመ። ጸሃፊዉም ወደ ብልጽግና መንገድ የሚያስገቡ አስተሳሰብ መርሆችን 13 መርሆችን በመጠቀም እንዴት ማሳካት እንደሚቻል ያሳየናል።
13 የብልጽግና አስተሳሰብ መርሆችም እንደሚከተሉት ናቸዉ።

መርህ 1. ጠንካራ ፍላጎት (Desire)
እንዲሳካለት የሚፈልግ ማንኛዉም ሰዉ በዉስጡ ካለዉ የተሻለ ደረጃ ላይ የመድረስ ጠንካራ ፍላጎት ሊኖረዉ ይገባል። ጠንካራ ፍላጎት የሌለዉ ሰዉ በምኞት ብቻ የፈለገበት መድረስ ላይሆንለት ይችላል። ጠንካራ ፍላጎት የሌለንን ነገር ወደ መኖር ለማምጣት የሚያስፈለግ የሚቀጣጠል ዉስጣዊ ሃይል ሲሆን፣ ባዶ ምኞት ግን የሌለንን ነገር በማሰብ ተስፋ እንድናጣ የሚያደርግ ነዉ። ስለ ጠንካራ ፍላጎት በመጽኃፉ ከተካተተ ታሪክ የጦር መሪዉን ሄርናን ካርቴዝ ተጠቅሷል።
በ 16ኛዉ ክፍለ ዘመን ሄርናን ኮርቴዝ የተባለ አንድ የጦር መሪ ወደ ሜክሲኮ በማቅናት ባራክሩዝ የተባለን ቦታ ለመዉረር በመርከብ በሄደበት ወቅት የጠበቀዉ የጠላት ጦር በጣም ብዙ እና አስፈሪ ነበር። በዚህም ምክንያት ወታደሮቹ የማቅማማትና ወረራዉን ትቶ የመመለስ ሃሳብ ሲያመጡ መሪዉም ሁሉም የመጡባቸዉን መርከቦች እንዲቃጠሉ አስደረገ። ከዚያም ወታደሮቹ ምንም አማራጭ ስላልነበራቸዉ ለነፍሳቸዉ ሲሉ ተዋግተዉ አሸነፉ። ከዚህም ታሪክ የምንረዳዉ ካፒቴይን ኮርቴዝ በዉስጡ ከነበረዉ የማሸኘፍ ጠንካራ ፍላጎት የተነሳ ወደ ኋላ የመመለስ ሃሳብ እንኳን እንዳይኖረዉ መርከቦችን እንዲቃጠሉ አስደርጓል። ይህም በዉስጡ የነበረዉ ጠንካራ የማሸኘፍ ፍላጎት እንጂ ምኞት አልነበረም። ስለዚህ ማንኛዉም መበልጸግ ወይም ያሰበዉን ማሳካት የሚፈልግ ሰዉ በዉስጡ ሊኖር የሚገባዉ ፍላጎት እንደ ኮርቴዝ ወደ ኋላ መመለሻ መርከቦቹን እስከማቃጠል መሆን አለበት።

አንድ ሰዉ በዉስጡ ያለን ፍላጎት ወደ ስኬት ለመቀየር ስድስት መራመድ ያለባቸዉ እርምጃዎች አሉ። ለምሳሌ የፈለገዉ የገንዘብ ብልጽግና ከሆነ፡-
1. ማግኘት የፈለገዉን ትክክለኛ የገንዘብ መጠን መወሰን
2. የፈለገዉን ለማግኘት እስከ ምን ድረስ እንደሚተጋ ማወቅ
3. መቼ ማግኘት እንደሚፈለግ የተቆረጠ የጊዜ ሰሌዳ ማስቀመጥ
4. ምን ሰርቶ እና እንዴት የሚፈልገዉን እንደሚያገኝ ጥርት ያለ እቅድ ማዉጣት እና መስራት መጀመር
5. ከላይ ያስመጣቸዉን ነገሮች ጥርት ያለ እቅድ መጻፍ (የፈለገዉን ትክክለኛ የገንዘብ መጠን፣ ምን ያህል ዋጋ እንደሚከፍል፣ መቼ ማግኘት እንደሚፈልግ፣ ምን ሰርቶ እንደሚያሳካ)
6. የጻፈዉን ዘወትር በቀን ሁለት ጊዜ ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነሳ እና ማታ ሊተኛ ሲል ማንበብ፣ በሚያነብበትም ወቅት ያቀደዉን እንዳሳካ እያሰበ መሆን አለበት።

መርህ 2. እምነት (Faith)
ስለነገሮች ያለን ጽኑ ፍላጎት ስር ሲሰድ እና ከጽኑ አስተሳሰባችን የሚመነጭ ስሜት ጋር ሲሆን እምነትን ይወልዳል። ፍላጎታችን እዉን እንዲሆን እንደሚሳካ የማይወላወል እምነት ያስፈልገናል።
95 በመቶ የሚሆነዉን ሃሳባችንን እና ድርጊታችንን የሚቆጣጠረዉ ከፊል ንቁ የአዕምሮአችን ክፍል sub concious mind የሚባለዉ ሲሆን አብዛኛዉን ጊዜ በልምድ እና ባጋጠሙን ሁኔታዎች ድግግሞሽ ይማራል። ስለዚህ በራሳችን እምነት እንዲኖረንም ሆነ ፍላጎታችንን ለማሳካት ትክክለኛ የህይወታችን ግብ መሆኑን አዕምሮአችን እንዲያምንበት ለ ለከፊል ንቁ አእምሯችን ማረጋገጫ እና የተደጋገመ ትዕዛዝ መስጠት ወይም ማስተማር ያስፈልጋል። ብዙ ጊዜ እንደሚታወቀዉ “ማየት ማመን ነዉ!” የሚለዉ ብሂል በ “ማመን ማየት ነዉ” ይተካል ማለት ነዉ።
ይህም የብልጽግና ሃሳብን አዕምሮአችን ላይ የምንቀርጽባቸዉ ሁለቱን የመጀመሪያ ክፍሎች በመዉሰድ ሶስተኛዉ እና ሃሳባችንን ወደ ድርጊት ወደምንቀይርብት ክፍል ያመራናል።

መርህ 3. ግለ አስተያየት (Auto Suggestion)
ግለ አስተያየት በስሜት ህዋሶቻችን የምንቀበላቸዉን መረጃዎች በጥቅል ሲገለጹ ማለት ነዉ። ግለ አስተያየት ነገሮችን በፍጥነት የምናስተዉልበትን ንቁ ወይም Conscious Mind እና መሰረታዊ አስተሳሰባችን የሚቀረጽበትን ከፊል ንቁ የሆነዉን የአዕምሯችንን ክፍል (Sub Conscious Mind) የምናገናኝበት ድልድይ ነዉ። ማንኛዉም አይነት ሃሳብ ከንቁ ወደ ከፊል ንቁ የአዕምሯችን ክፍል መሸጋገር ሲችል ለዘላቂ አስተሳሰባችን እና አመለካከታችን መሠረት ይጥላል። ብዙ ጊዜ ምኞቶቻችን እንደማይሳኩልን እና ዋጋ እንደሌለን፤ ያለንበት አከባቢ፣ ሁኔታ ወይም አጠገባችን ያሉ ሰዎችም ቢሆኑ የሚነግሩን እና ያም ትክክል እንደሆነ ማሰባችን ፍላጎታችን እንደማይሳካ አምነን እንድንቀመጥ ሊያደርገን ይችላል። ነገር ግን ከላይ ያየናቸዉን ሁለት ክፍሎች (ፍላጎት እና እምነትን) በመጠቀም ከፊል ንቁ የአዕምሯችንን ክፍል የራሳችንን ጊዜ በመዉሰድ ደጋግመን ለራሳችን በመንገር እና በማስተማር የስኬታችንን እዉንነት ልናሳምነዉ እንችላለን። በምናደርገዉ ነገር ሁሉ የእቅዳችን መሳካት እንዲያስደስተን እና ግባችንን ከሃሳባችን ጋር የተቀናጀ በማድረግ ጉዞአችን ሁሉ ወደ ፍላጎታችን መሳካት እንዲሆን እና አዕምሮአችንም ሁሌ እሱን እንዲያስብ ማድረግ እንችላለን። በዚህም ምክንያት ከፊል ንቁ አዕምሮአችንም የምናደርጋቸዉን ነገሮች ሁሉ ከግባችን አንጸር በመመዘን ጊዜ፣ ገንዘብ እና ጉልበታቸችንን ለማይረባ ነገር ማባከንን ትተን ለግባችን መሳካት እንድንጠቀምበት ይረዳናል።

መርህ 4. ልዩ እዉቀት (Specialized Knowledge)
ለብልጽግና መሰረቱ እዉቀትን መሰብሰብ ብቻ ቢሆን ኖሮ አብዛኞቹ ባለጠጎች የአለማችን ፕሮፌሰሮች ብቻ ይሆኑ ነበር። ስለብዙ ነገሮች ማወቅ ብቻ አንድን ሰዉ ብልህ እና ባለጠጋ ሊያደርገዉ አይችልም። ወደ ብልጽግና የሚያደርሰዉ ብዙ መረጃ መሰብሰብ ሳይሆን፣ የሰበሰብነዉን መረጃ ትርጉም ባለዉ መልኩ መጠቀም መቻላችን ነዉ። የሰዉ ልጅ በተፈጥሮ አንድ ነገር ብቻ አተኩሮ ሲሰራ ዉጤታማ ይሆናል። ለዚህም ነዉ የፎርድ መኪና ባለቤት ሄንሪ ፎርድ “ስለ ብዙ ነገር ራሴ ለመሆን ከምጥር ይልቅ ስለተለያዩ ነገሮች የሚያዉቁ ሰዎችን ባውቅ ይሻለኛል” ያለዉ። ይሄንንም ለመረዳት እንዲረዳን ሁለት አይነት የዕዉቀት አይነቶች እንመልከት። አንደኛዉ ጠቅላላ እዉቀት ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ አንድ ነገር ላይ ያተኮረ ወይም ልዩ እውቀት የምንላቸዉ ናቸዉ።
ጠቅላላ እዉቀት ስለ ብዙ ነገር ያለን እዉቀት ሲሆን ከዚህ ዉስጥም በጣም ጥቂቱ ከምንሰራዉ ስራ ጋር ተያያዥነት አለዉ።
ልዩ እዉቀት ድግሞ በፍላጎታችን እና ባተኮርነዉ ዘርፍ ላይ ተመስርተን የምናካብተዉ እዉቀት ነዉ። ስለዚህ ብዙ የጠቅላላ እዉቀት ከሚኖረን ይልቅ እቅዳችንን ለማሳካት የምንሰራዉ ስራ ላይ ጠለቅ ያለ እዉቀት ቢኖረን ይመረጣል።
እዉቀት ሃይል የሚሆነዉ ግልጽ በሆነ አላማ ዕቅድና የድርጊት መረሃ ግብር ሲደራጅ እና ሲመራ እና አቅጣጫ ሲሰጠዉ ብቻ ነዉ።

መርህ 5. ምናብ (Imagination)
ምናብ ፍላጎታችን፣ ሃሳባችንና እቅዶቻችን ቅርጽ የሚይዙበት የአዕምሯችን ቤተ ሙከራ ማለት ነዉ። ፈጠራዊ የሆነ ከፍላጎታችን አንጻር እቅዶቻችንን፣ የምንሄድበትን መንገድ እና ግባችንን የምናይበት ሲሆን ለፍላጎታቸን መሳካት ትልቅ ቦታ አለዉ። የሰዉ ልጅ በፈጠራዊ ምናቡ ማየት የቻለዉን ሁሉ መፍጠር ይችላል። ለምሳሌ ቶማስ ኤዲሰን አምፖል ለመስራት ብዙ ጊዜ ቢሞክርም ከሙከራዉ ይልቅ ከባዱ የአምፖልን ሃሳብ ማምጣቱ ነበር። አንዴ ያንን ምናባዊ ሃሳብ ካመጣ በኋላ ግን በምናቡ ያየዉን መፍጠር ችሏል። ስለዚህ ፍላጎቱን በምናቡ ማየት የቻለ፣ ያኔ በእዉኑ ለመፈጸም አይቸገርም።

መርህ 6. የተደራጀ እቅድ (Organized Planning)
ፍላጎታችን እንዲሳካ የተደራጀ ዕቅድ መወጠናችን የስኬታችንን ሁኔታ የላቀ ያደርገዋል። በመጀመሪያዉ መርህ ላይ ያሰብናቸዉን አቀናጀተን በማስቀመጥ በቀላሉ ወደ ስኬት መቀየር የሚችል እቅድ ማድረግ ይኖርብናል። ይሄንንም ለማድረግ ልንከተለዉ የሚገባ መንገድ፡-
1ኛ. አላማችንን እንድናሳካ ሊረዱን የሚችሉ ሰዎችን በመሰብሰብ ህብረት መመስረት
2ኛ. ለእያንዳንዱ የህብረቱ አባል ምን መስጠት እንደምንችል ማሰብ
3ኛ. እቅዳችንን ሙሉ በሙሉ እስክንጨርስ ድረስ በተደጋጋሚ ከህብረቱ አባላት ጋር በመገናኘት መስራት እና
4ኛ. ከህብረቱ አባላት ጋር ጥሩ መስተጋብር መፍጠር
እነዚህን መንገዶች በመመከተል፣ እቅዳችን ጠንካራ እና ጊዜ ተሻጋሪ እንዲሆን ማድረግ እንችላለን። እቅዳችንንም በየጊዜዉ መገምገም እና መስተካከል ያለበትን ወይም መታደስ ያለበትን ነገር ከቡድኑ አባላት ጋር በመሆን ማደስም ያስፈልጋል።

መርህ 7. ዉሳኔ (Decision)
በአሜሪካ ዉስጥ በ25, 000 ዉድቀት በህይወታቸዉ ባጋጠማቸዉ ሰዎች ላይ በተደረገዉ ጥናት ከ 30 የዉድቀት ምክንያቶች መካከል የዉሳኔ አወሳሰድ ድክመት ከግንባር ቀደም የዉድቀት ምክንያቶች መካከል ተጠቅሷል። ዉሳኔ ለመወሰን መቸገር እና በወሰኑት ዉሳኔ ጸንቶ እስከመጨረሻዉ ያለመጓዝ ወይም በየጊዜዉ በደምብ ሳያገናዝቡ ዉሳኔ መቀያየር የብዙዎቹ ብልጽግና መንገድ ጀማሪዎች ዉድቀት ምክንያቶች ናቸዉ።
አብዛኞቹን ባለጠጎችን የሚያመሳስላቸዉ ነገር ዉሳኔን ለመወሰን ፈጣን በመሆናቸዉ በአቅራቢያቸዉ የሚገኙ ሁኔታዎችን መጠቀም መቻላቸዉ ነዉ። ይሄንንም ለማድረግ ቶሎ ይወስናሉ እንደ አስፈላጊነቱም በጥናት ላይ ተመስርተዉ ዉሳኔያቸዉን መቀየር ካለባቸዉ ይቀይራሉ፣ ነገር ግን በመሰኑት ዉሳኔ መጨረሻቸዉን ማየት ይችላሉ።

መርህ 8. ጽናት (Persistence)
ጽናት ማለት ፍላጎትን ለማሳካት በሚደረግ ጉዞ፣ ከመንገድ ሳይወጡ ወይም ሳያቋርጡ መቆየት ነዉ። ጽናት ለብልጽግና ከሚደረግ ጥረት ዉስጥ ቁልፉን ሚና ይጫወታል። የአላማ ጽናትን ለማዳበር ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። በመንገዳችን በመጽናታችን በዉስጣችን ያለዉ ፍላጎት ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ማወቅ ይቻላል። ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነዉ ኮሎኔል ሳንደርስ ሲሆን የ KFC ባለቤት ነዉ። ይህ ሰዉ ስኬታማ ከመሆኑ በፊት ከአንድ ሺህ ጊዜ በላይ የወደቀ ቢሆንም በመንገዱ ላይ የነበረዉ ጽናት ግን ተስፋ ቆርጦ በወደቀበት እንዳይቀር እና ፍላጎቱን ለማሳካት ደግሞ ደጋግሞ እንዲሞክር አድርጎታል። ስለዚህ የምንፈልገዉን እስክናገኝ ድረስ ምንጊዜም ደግመን ደጋግመን የመሞከር እና በአላማችን ጸንተን መጓዝ ሊኖርብን ይገባል።

መርህ 9. የላቀ አዕምሮ ሃይል (The Power of Master Mind)
ወደ ብልጽግና በምንሄድበት መንገድ ሃይል አስፈላጊ ነገር ነዉ። እቅዶቻችን ያለ ሃይል ምንም ጥቅም የላቸዉም። በዚህ አገባብ ሃይል ማለት በብልሃት የተደራጀ እና አቅጣጫ የተቀመጠለት ዕዉቀት ማለት ሲሆን ይህም ማለት የሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎችን የተቀናጀ ትጋት ነዉ። ይህም ሃይል ወደ ብልጽግና የምናደርገዉን ጉዞ የሚያቀልልን እና ያገኘነዉንም ስኬት ቀጣይነት እንዲኖረዉ አስተዋጥኦ ያለዉ ነዉ። ማንኛዉም ሰዉ ቢሆን ይሄንን ብቻዉን ለማድረግ በሚሞክርበት ወቅት የማሳካት አቅሙ በጣም ትንሽ ነዉ። ነገር ግን በሁለት እና ከዚያ በላይ ባሉ ተመሳሳይ አላማ አንግበዉ በሚጓዙ ሰዎች መሃል በሚፈጠር ህብረት ከህብረቱ አባላት ከሚመጣ ሀይል በተጨማሪ የአንድነታቸዉ መስተጋብር የሚፈጥረዉ ሌላ ሶስተኛ ሃይል መኖሩ ለስኬት የሚያደርጉትን ጉዞ ያፋጥነዋል። ነገር ግን አብረናቸዉ የምንሆናቸዉ ሰዎች በተመሳሳይ እይታ ካልሆኑ እና ጉልበታችንን የሚጨርሱ እና ወደ ኋላ የሚጎትቱን እንዳይሆኑ ሰዎችን በጥንቃቄ መምረጥ አለብን።

መርህ 10. ወሲባዊ ስሜትን ወደ ሃይል የመቀየር ሚስጥር (Transmutation)
መጽሃፉ ስለ ብልጽግና አስተሳሰብ መርሆች እንጂ ስለወሲባዊ ግኑኝነት የሚተነትን አይደለም። ይሄኛዉ መርህ ለመረዳት ግር የሚል ቢመስልም ተፈጥሮ ያደለንን ጠንካራ እና ገዢ የሆነዉን የወሲብ ስሜት በአግባቡ በመግራት እና ወደ ፈጠራዊ ምናብ ሃይል በመቀየር ለስኬታችን እንዲዉል ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ ይነግረናል። ወሲባዊ ስሜትን መግራትና በምንፈልገዉ መልኩ መጠቀም የሚለዉ አስተሳሰብ ከጥንት ጀምሮ በተለይም በምስራቃዊ የአለማችን ክፍሎች ሲተገበር የቆየ ቢሆንም በሰፊዉ አይታወቅም። አዕምሯችን በቶሎ መልስ ከሚሰጣቸዉ ቀስቃሽ ነገሮች መካከል ወሲባዊ ስሜት ቀዳሚዉና ከፍተኛ ሃይል ያለዉ ነዉ። የሰዉ ልጅ ፍትወታዊ ፍላጎት በሚያድርበት ጊዜ ፍላጎቱን ለማሳካት በሌሎች ጊዜያት የማያሳየዉን ብርታት፣ ቁርጠኝነት እና ጽናት እና አስተሳሰብ ይተገብራል። ወሲባዊ ፍላጎት ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ የሰዉ ልጆች ክብራቸዉን እና ህይወታቸዉን ሳይቀር አሳልፈዉ ለርሱ ይሰጣሉ። ይሄንን ፍላጎት፣ ሃይል በፈለግነዉ መልኩ የብልጽግና አላማችንን ለማሳካት ልንጠቀምበት ብንችልስ? ማንኛዉም ሰዉ ፍትወታዊ ስሜቱን ለማርካት የሚጥረዉን ያህል በስራዉ ላይ ዉጤታማ ለመሆን ቢደክም የት መድረስ ይቻል ነበር። ወሲባዊ ፍላጎት ተፈጥሯዊና ስንወለድ ጀምሮ አብሮን የሚቆይ ዉስጣዊ ስሜት ሲሆን ይህ ስሜት ሊወገድም ሆነ ሊገታ አይችልም። ነገር ግን ሌላ መዉጫ ሊበጅለት ይችላል። ሌላ መዉጫ ሲባል ሰዉነትን አዕምሮንና መንፈስን በጋራ ወደሚያጎለብት ስሜታዊ ሀይል መቀየር ማለታችን ነዉ። ይሄንን ሃይል ለስኬታችን መጠቀም እንዴት እንችላለን የሚለዉን ጥያቄ ስናነሳ የፍትወትን ስሜት ለማርካት ሰዎች የተለያዩ መንገዶችን የግድ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ሁሉ ያንን አጋጣሚ ላበጀንለት አላማ ፈጠራዊ ምናብ ሃይል እንዲሆንን ብንጠቀም ሃይሉን ለስኬታችን እንደ ግብዓት ልንጠቀመዉ እንችላለን ማለት ነዉ። ስለዚህ ወሲባዊ ስሜትን ወደ ሌላ ገንቢ ሃይል ለመለወጥ መደረግ ካለባቸዉ እርምጃዎች ጤናማ የወሲብ ህይወት መምራት አንዱ ነዉ። ከመጠን ካለፈ የአዕምሮአችን የመፍጠር አቅም ሊያዳክም ይችላል። ስለዚህ የተለያዩ የወሲብ ስሜት ማርኪያ የሆኑትን ለምሳሌ፡- ፖርኖግራፊ (የወሲብ ፊልሞችን ማየት) ወይም ግለወሲብ መተግበር የአዕምሯችንን አቅም ከማሳጣቱም በላይ ለራሳችን ያለንን ክብር ያወርደዋል። ስለዚህ ይህ ስሜት በሚመጣበት አጋጣሚ ወደ ስራ መመለስ፣ ስለ አላማችሁ ማሰብ የስሜቱን ሃይል ለጥቅም እንድታውሉት ይረዳችኋል ማለት ነዉ። ይሄንንም ድርጊት እየለመዳችሁት ስትሄዱ ዉጤታማ እየሆናችሁ ትሄዳላችሁ ማለት ነዉ። ከዚያም በመቀጠል ሙሉ ትኩረትን አላማችን ላይ ማድረግም ወደ ዉጤታማነት ያደርሰናል።

መርህ 11. ከፊል ንቁ የአዕምሯችን ክፍል (Subconscious Mind)
ከፊል ንቁ የሆነዉ የአዕምሯችን ክፍል በአምስቱ የስሜት ህዋሶቻችን የሚገቡ የተለያዩ ሃሳቦች እና መረጃዎችን ይመዘግባል ያስቀምጣል። አመለካከቶቻችን የቆዩ ትዉስታዎቻችን ከዚህ ክፍል አዉጥተን የምንጠቀምባቸዉ ናቸዉ። በዚህም 95 በመቶ የሚሆነዉን የእለተዕለት ማሰብ ስራችንን የሚሰራዉን የአዕምሮ ክፍላችንን በመቆጣጠር እና ወደ አዕምሯችን የሚገቡትን ሃሳቦች በመጠንቀቅ ወደ ስኬት በምናደርገዉ ጉዞ ሁልጊዜ ገንቢ ሃሳቦችን ማምጣት እና ለእርሱም ተገዢ መሆን እንችላለን። ጥሩ ወይም ገንቢ ስሜቶች እና አመለካከቶች በአዕምሯችን የበላይ ማድረግ የሁሉም ሰዉ የየራሱ ሃላፊነት ነዉ። ለሰዉነት የምንመገበዉን ምግብ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ሁሉ ለምናያቸዉ፣ ለምንሰማቸዉ እና ወደ አዕምሯችን ለሚገቡ ሃሳቦችም በጥንቃቄ ከአላማችን አንጻር በመምረጥ ይሄንን ክፍል በመቅረጽ ለስኬታችን ማዋል እንችላለን። ስለዚህ ዋነኞቹን አዎንታዊ ስሜቶችን ማለትም ጠንካራ ፍላጎት፣ ጽኑ እምነት፣ ዉስጣችንን እንዲቆጣጠሩ በማድረግ ወደ ስኬታችንን የምንሄድበትን ጉዞ ማፋጠን እንችላለን።

መርህ 12. አዕምሮ (Brain)
አዕምሮ የሃሳባችን ማሰራጫ እና መቀበያ ጣቢያ ሲሆን የተለያዩ አዳዲስ ሃሳቦችን ያስተናግዳል። አስተሳሰባችንንም ያሰራጫል። ፍላጎታችንን አላማችንና እቅዳችንን በጽኑ እምነት ከራሳችን ጋር ካዋኸድናቸዉ በኋላ ወደ ተግባር የምንለዉጥበት እና የምናሰራጭበት የአእምሯችን ቦታ ከፊል ንቁ የሆነዉ ክፍል ነዉ። የፈጠራ የምናባችን ክፍል ደግሞ ፍላጎታችን እና እቅዳችንን የሚቀበል የአዕምሯችን ክፍል ነዉ። የፈጠራ ምናባችን ሃሳብ የሚቀበለዉ በዙሪያዉ ከሚያስተዉላቸዉ ነገሮች በመነሳት ነዉ። ነገር ግን እኛን ለዉጤታማነት የሚያበቁ አዳዲስ ሃሳቦችን ለማፍለቅ አርቴፊሻል የምናባችንን ክፍል በአብዛኛዉ እንደምንጠቀም መርሳት የለብንም። ይህ ማለት በዙሪያችን ከምናስተዉላቸዉ ነገሮች በመነሳትና አርቴፊሻል ምናባችንን በመጠቀም አዲስ ሃሳብ ማመንጨት እንችላለን ማለት ነዉ። ስለዚህ የግል አስተያየት መርህን በመተግበር አዕምሯችን ስራ እንዲጀምር በማድረግ ወደ ማሰራጫ ጣቢያ አዳዲስ ሃሳቦችን በማድረስ የአዕምሮአችንን አቅም በመጠቀም ወደ ብልጽግና የምንሄድበትን ጉዞ ማሳለጥ ይቻላል።

መርህ 13. ስድስተኛዉ የስሜት ህዋስ (Sixth Sense)
ስድስተኛዉ የስሜት ህዋስ የዕውቀት መግቢያ በር የሚባል ሲሆን ያለምንም ጥረት እና ልፋት ከምድራዊ እዉቀቶች ጋር ግኑኝነት መፍጠር የሚያስችለንን ብቃት የሚሰጠን ነዉ። ይሄንን መርህ ለመተግበር ከላይ ያሉት 12 መርሆች ላይ ብቁ መሆን ያስፈልጋል። ይሄዉም የስሜት ህዋሳችን የፈጠራ የምናባችን ክፍል ነዉ። በሌላ መልኩ 99 በመቶ ትክክለኛ የሆነ ደመ ነፍስ፣ ግምት ወይም ትንበያ ማለት ነዉ። ሰዎች ቀልቤ ነግሮኛል በማለት የሆነን ሁኔታ በትክክል የሚሰማቸዉ በዚሁ ህዋስ ነዉ። ይህ ስሜት የሚኖረን ከሆነ ለዉጤታማነት በምናደርገዉ እንቅስቃሴ ዉስጥ ሊሰጠን የመሚችለዉ ጠቀሜታ የጎላ ነዉ። ስድስተኛዉን የስሜት ህዋስ ለመረዳት ከራስ ጋር የጥሞና ጊዜ በማሳለፍ የሚመጣ የአዕምሮ ብስለት ያስፈልጋል። የሄንን ሃይል ለመጠቀም ሌሎችን መርሆች በአግባቡ በመተግበር ቀስ ብሎ በሂደት የሚመጣ ነዉ።
አመሰግናለሁ።

Continue Reading
You may also like...

MD, Lecturer, UX & UI Developer, Consultant SMM, and Blogger.

Click to comment

More in ካነበብኳቸዉ

To Top