fbpx
Connect with us

የሆድ ድርቀት መፍትሄዎች

featured
Pixabay

ህክምና

የሆድ ድርቀት መፍትሄዎች

የሆድ ድርቀት የደረቀ አይነምድርን ወይም አይነምድር ለማስወገድ መቸገርን የሚገልጽ ነዉ።የሆድ ድርቀት አይነምድር በሚወገድበት ጊዜ ህመም መፈጠርን፣ ለረጅም ጊዜ ቢያምጡ እንኳ የአይነ ምድር አለመዉጣት ወይም ከሶስት ቀናት በላይ አይነምድር ሳያዩ መቆየትን ሊያካትት ይችላል።
የሆድ ድርቀት አንጻራዊ ስያሜ ሲሆን ጤነኛ የሚባለዉ የአይነ ምድር አወጣት ልማድ ከሰዉ ወደ ሰዉ እጅጉን ሊለያይ የሚችል ነዉ። በየቀኑም አይነምድር ላይታይ ይችላል። አንዳንድ ጤነኛ ሰዎች አይነምድራቸዉ ሁል ጊዜ ቀጠን ያለ ሌሎች ደግሞ ጠጣር ሆኖ ለማስወጣት ግን የማይቸገሩ ሊሆኑ ይችላሉ።

አንድ ሰዉ አይነ ምድሩ ጠጣር ከሆነ፣ በረጅም ጊዜ ማለትም ቢያንስ ሶስት ቀን ቆይቶ የሚመጣና ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ወይም ማማጥ የሚያስፈልገዉ ከሆነ የሆድ ድርቀት አለባቸዉ ይባላል። ትልቅ እና ሰፊ የደረቀ አይነምድር የፍንጢጣ ሽፋን ሊቀድ ይችላል። ይህ ደግሞ በተራዉ የፊንጢጣ መሰንጠቅ ሊያስከትል ይችላል።

የሆድ ድርቀት መንስኤዉ ምንድነዉ?

 • የፋይበር ይዘታቸዉ ዝቅተኛ የሆኑ ምግቦችን በመመገብ
 • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያለመስራት
 • በቂ ዉሃ ያለመጠጣት
 • አይነምድር ወጥሮት ሳለ ቶሎ ያለማስወጣት ወይም መዘግየት
 • ዉጥረት
 • የተለያዩ ህመሞች ለምሳሌ፡- የአንጀት ህመም፣ እርግዝና፣ የታይሮይድ እጢ ከመጠን በታች መመረት፣ የነርቭ ህመሞች እና የተለያዩ የአንጀት እንቅስቃሴን የሚቀንሱ መድሃኒቶች ይገኙበታል

ምን ማድረግ አለብኝ?
በምግብ ዉስጥ በቂ ፋይበር እንዲኖር ማድረግ ይገባል። ትኩስ ወይም ያልቆዩ ፍራፍሬዎችን፣ በፋብሪካ ፕሮሰስ ያልተደረጉ የስንዴ ምግቦች ማለትም ቤት ዉስጥ ተፈጭቶ የተዘጋጀ የስንዴ ዳቦ ወይም ምግብ፣ አጃ እና ጥራጥሬዎች ጥሩ የፋይበር ምንጮች ስለሆኑ አዘውትሮ መመገብ ይመከራል። በፋይበር የበለፀጉ ምግቦች በተጨማሪ በቂ ዉሀ መጠጣት አይነምድር በቀላሉ ለማስወጣት ይበልጥ ይረዳል።
መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጤነኛ የአይነምድር አወጣጥ ይኖርዎ ዘንድ ያግዛል። መራመድ የማይችሉ (wheelchair የሚጠቀሙ ወይም አልጋ ላይ የሚዉሉ) ከሆኑ የአቀማመጥ ወይም አተኛኘት አቅጣጫን ቶሎ ቶሎ በመቀየር፣ ሆድ አኮማታሪ እንቅስቃሴዎችን መስራት እና እግርዎን ማንሳት ይኖርብዎታል። ካለብዎት አካላዊ ጉድለት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምን አይነት እንደሆነ ሃኪምዎን ማማከር ይችላሉ።

አይነምድር አለስላሽ (Stool Softners) መድሃኒቶች ለሆድ ድርቀት ችግር ጠቀሜታ ሊኖራቸዉ ይችላል። በተጨማሪም የተስተካከለ የአይነምድር አወጣጥ ይኖር ዘንድ የሚረዱ መድሃኒቶች መጠቀም የሚገባቸዉ ግን ከበድ ያለ የሆድ ድርቀት ችግር ያለባቸዉ ብቻ ናቸዉ። በተጨማሪም እነዚህን መድሃኒቶች ተጠቃሚዉን ጥገኛ የማድረግ ዝንባሌ ስላላቸዉ ለረጅም ጊዜ መዉሰድ አይመከርም።

ሀኪም መቼ ነዉ ማማከር ያለብኝ
የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ወደ ሃኪም ቤት በመሄድ ዶክተርዎን ያማክሩ።

 • የሆድ ቁርጠት፣ ጋዝ ወይም አይነምድር ማስወጣት አለመቻል ከድንገተኛ የሆድ ድርቀት ጋር ከተከሰተ
 • ሀይለኛ የሆድ ህመም በተለይም ከሆድ መነፋት ጋር ከተከሰተ
 • ደም የተቀላቀለበት አይነምድር
 • የሆድ ድርቀት እና ተቅማጥ መፈራረቅ
 • ቀጭን እና ጠቆር ያለ አይነ ምድር መታየት
 • የፊንጢጣ ህመም
 • መንስኤዉ ያልታወቀ የሰዉነት ክብደት መቀነስ
 • ከ 5 ቀናት ያለፈ አይነምድር አምጪዎችን ተጠቅመዉ ወይም የግል እንክብካቤ አድርገዉ ለዉጥ ካልተገኘ

አመሰግናለሁ።

Continue Reading

MD, Lecturer, UX & UI Developer, Consultant SMM, and Blogger.

1 Comment

More in ህክምና

To Top