fbpx
Connect with us

የስኳር ህመም ሲጀምር የሚታዩ 9 ምልክቶች

feautured

ህክምና

የስኳር ህመም ሲጀምር የሚታዩ 9 ምልክቶች

የስኳር በሽታ በሰውነትዎ ውስጥ ኢንሱሊን የማምረት ወይም ጥቅም ላይ የማዋል ችሎታ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር በሽታ ሲሆን ይህም በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከፍተኛ በማድረግ የተለያዩ የሰዉነት ክፍሎችን ለጉዳት ይዳርጋል ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች በጣም ስውር ሊሆኑ ስለሚችሉ አንዳንድ ሰዎች ልብ ሳይሏቸዉ ህመሙ በሰዉነታቸዉ ስር ይሰዳል፡፡ የስኳር በሽታ ሕክምና ካልተደረገለት ጤናን ማቃወስ ብቻ ሳይሆን ዕድሜም ሊያሳጥር ይችላል ፣ ለዚህም ነው ቶሎ በሽታውን በመለየት አስፈላጊዉን ክትትል ማድረግ በጣም አስፈላጊ የሚሆነው ፡፡
ከሚከተሉትን 9 ምልክቶች በሰዉነትዎ ካስተዋሉ የስዃር ህመም ሊሆን ስለሚችል ምርመራ በማድረግ መለየት ተገቢ ነዉ።

1. እጅግ የበዛ የዉሃ ጥማት እና ሽንት
ከፍተኛ የዉሃ ጥማት (polydipsia) እና ቶሎ ቶሎ ሽንት መምጣት (polyuria) የስኳር ህመም ላይ እጅግ በጣም የሚታዩ ምልክቶች ናቸዉ። የስዃር ህመም በሚከሰትበት ጊዜ በደማችን ዉስጥ ያለዉ የስኳር መጠን እጅግ ከፍ ስለሚል ኩላሊታችን ደምን በሚያጣራበት ጊዜ ከመጠን በላይ የሆነዉን ስኳር ወደ ሰዉነት አጣርቶ ማስቀረት ስለማይችል በሽንት እንዲወገድ ይሆናል። ከፍተኛ ስኳር በሽንት ከሰዉነታችን በሚወጣበት ጊዜ በሰዉነታችን ያለዉንም ዉሃ አብሮ እንዲወገድ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ ሰዉነታችን እንዲደርቅ እና እንዲጠማን ስለሚያደርገን ብዙ ዉሃ እንድንጠጣ እንገደዳለን፣ ይሄም ደግሞ የባሰ ሽንት በተደጋጋሚ እንዲመጣ ምክንያት ይሆናል።

2. ከባድ የረሃብ ስሜት
ከባድ የረሃብ ስሜት እና ብዙ ምግብ መመገብ (Polypagia) ከከፍተኛ የዉሃ ጥም እና ተደጋጋሚ የዉሃ ሽንት መወጠር ጋር በመሆን አንድ ላይ ሶስቱ ዋነኞቹ የስኳር ህመም ምልክት ድርሻን ይይዛሉ። በስዃር ህመም ጊዜ የበላነዉ ምግብ ወደ ግሉኮስ ከተቀየረ በኋላ ወደ ህዋሳት እንዲገባ የሚያስችለዉ ኢንሱሊን ስራ ስለሚስተጓጎል ምንም ያህል ብንበላ ምግቡ ህዋሳቱ ጋር ስለማይደርስ የረሀብ ስሜት አይጠፋም። ይልቁንም ይበልጥ ብዙ መብላታችን በደማችን ዉስጥ የሚኖረዉን የስዃር መጠን ከፍ ከማድረግ የዘለለ ለሰዉነታችን ጥቅም አይኖረዉም።
ስለዚህ ምግብ በበቂ ሁኔታ እየተወሰደ ይልቅ ረሃብ ስሜት ከወትሮዉ የተለየ ሲሆን ሌሎቹ ምልክቶች ባይኖሩ እንኳን በሃኪም መታየቱ መልካም ነዉ።

3. ዘላቂ የድካም ስሜት
ሌላኛዉ የስኳር ህመም ምልክት የማያቋርጥ ድካም ነው ፡፡ የስኳር ህመም ሲኖርዎ ሁል ጊዜ በሚራቡት ተመሳሳይ ምክንያት ሁል ጊዜ ድካም እና እንቅልፍ ይሰማዎታል፣ ህዋሳትዎ ለኃይል የሚጠቀሙበት ግሉኮስ የላቸውም ፡፡ በተደጋጋሚ በሽንት ምክንያት የሚፈጠረው ድርቀትም ለድካም ስሜት አስተዋጽኦ ያደርጋል ፡፡
የድካም ስሜት የብዙ ሌሎች ሁኔታዎች ምልክት ሊሆን ይችላል ፣ አንዳንዶቹም የሕክምና (ከፍተኛ ሃይል የያዙ ምግቦችን በብዛት መመገብ፣ በጣም ብዙ አነቃቂ ነገሮችን መዉሰድ ፣ እርጅና) ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ዝርዝር ዉጪ ከሌሎች ምልክቶች ጋር ሲደባለቅ ዘላቂ የድካም ስሜት የስኳር በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል ፡፡

4. የደበዘዘ እይታ
የደበዘዘ እይታ በጣም የከፋ የአይን ችግር ምልክት በማይሆንበት ጊዜ የስኳር በሽታ የመጀመሪያ ምልክት ሊሆን ይችላል ፡፡ በስኳር ህመም ጊዜ የአይን ብዥታ የሚከሰተው በዓይን ዉስጥ ያሉ ፈሳሾች በደም ዉስጥ ካለዉ ከፍተኛ የስኳር መጠን የተነሳ በሚከሰተዉ ለዉጥ ምክንያት ነው ፣ ይህም የአይንዎን ሌንስ እንዲያብጥ እና ቅርጹን እንዲቀይር ያደርገዋል ፡፡ ይህ የማተኮር ችሎታዎን ይጎዳል ፣ እይታዎም ላይ ብዥታ ይፈጠራል። ይሄም ለዉጥ የደም የስኳር መጠን በሚስተካከልበት ጊዜ ሊስተካከል የሚችል ሲሆን ስኳሩ ካልተስተካከለ እየባሰ የሚሄድ እና እስከ አይነስዉርነት ሊዳርግ የሚችል ነዉ።

5. ምክንያቱ ያልታወቀ ክብደት መቀነስ
ያልታወቀ ክብደት መቀነስ ማለት ያለ አመጋገብ ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እገዛ ብዙ ክብደት መቀነስ ማለት ነው፡፡ የስኳር በሽታ በሚኖርበት ጊዜ ሰውነትዎ የግሉኮስን የኃይል ምንጭ አድርጎ መጠቀም ስለማይችል በምትኩ የሰዉነት ስብ እና ጡንቻን ለኃይል ማቃጠል ይጀምራል ፣ በዚህም ክብደትዎ እንዲቀንስ ያደርገዋል ፡፡ ሰውነትዎ ሽንት ለማምረት የሚገኘውን ሁሉንም ፈሳሾች ስለሚጠቀም የሰዉነት ድርቀትም ለድንገተኛ ክብደት መቀነስ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ያልተጠበቀ የክብደት መቀነስ በብዛት የ 1 ኛ ዓይነት የስኳር በሽታ የመጀመሪያ ምልክት ቢሆንም በሁለተኛዉም የስኳር ህመም የሚሰቃዩ ሰዎችም ላይ ሊታይ ይችላል።

6. የሰዉነት ማሳከክ
ከላይ እንደተጠቀሰው ከመጠን በላይ ስኳር በሽንትዎ በሚወጣበት ጊዜ ቆዳዎን (ትልቁን አካልዎን) ጨምሮ ከሌሎቹ ሕብረ ሕዋሳትዎ የሚወስዱ ፈሳሾችን ይወስዳል ፡፡ ደረቅ ቆዳ ሊያሳክክዎት ይችላል ፣ እና እነዛን የደረቁ ቆዳ መቧጠጥ ቆዳዎን እንዲሰበር ከዚያም አልፎ ተርፎም ለኢንፌክሽን ሊያጋልጥ ይችላል። ለቆዳ ማሳከክ ሌላው ምክንያት የፈንገስ ኢንፌክሽኖች ሲሆኑ ይህም የስኳር ህመም ባለባቸው ሰዎች ላይ በብዛት የሚታይ ነዉ።

7. የቁስል ቶሎ ያለመዳን
በጣም በዝግታ የሚድኑ ቁስሎች ብዙውን ጊዜ የስኳር በሽታ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። በደም ውስጥ ያለው ከፍተኛ የስኳር መጠን በቁስሎች ላይ እብጠትን ከመጨመር በተጨማሪ ደካማ የደም ዝውውርን ያስከትላል ፣ ይህም ደሙ የተጎዱትን የቆዳ አካባቢዎች መድረስ እና መጠገን ከባድ እንዲሆን ያደርጋል። ይህ በተለይ እግር ላይ የሚከሰት ሲሆን የስኳር በሽታ ላለባቸው ህመምተኞች ደግሞ ወደ ከባድ ችግሮች የሚያመራ የእግር ቁስለት መከሰቱ አሳሳቢ ጉዳይ ነዉ።
ስለዚህ በሰዉነት ላይ ያለ ቁስልዎ ከወትሮ በተለየ ለመዳን የሚቆይ ከሆነ የስኳር ህመም ምልክት ሊሆን ስለሚችል መመርመሩ አስፈላጊ ነዉ።

8. የቆዳ ላይ ጥቁረቶች
ይህ በቆዳ ላይ የሚከሰት ጥቁረት ወይም አካንቶሲስ ንግሪካን ተብሎ የሚጠራዉ በቆዳ ላይ ራቅ ራቅ ብሎ ወደ ሻከራነት እና ወደ ጥቁረት በመቀየር የሚታይ የቆዳ ሁኔታ ነው። እነዚህ ጥቁረቶች ብዙ ጊዜ ቆዳ በሚታጠፉባቸው ቦታዎች ላይ በብዛት ይታያሉ-በአንገት ላይ ፣ በብብት ላይ ፣ በወገብ ላይ ፣ በክርንዎ ውስጥ ፣ ከጉልበቶች በስተጀርባ እና በጣቶች አንጓዎች ላይ ሊታዩ ይችላሉ።
እነዚህ ጥቁረቶች ብዙ ጊዜ የቅድመ ስኳር ህመም ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ በሃኪም መታየቱ መልካም ነዉ።

9. የእጅ ወይም እግር መደንዘዝ
በእጆች ወይም በእግር ( በእጅ ጣቶች ወይም በእግር ጣቶች) ላይ ድንዛዜ ፣ መንቀጥቀጥ ፣ ወይም ህመም ሌላው የስኳር በሽታ ምልክት ነው ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ከፍ ያለ የደም ስኳር ወደ ደካማ የደም ዝውውር ይመራል ፣ ያ ደግሞ በምላሹ የነርቭ ጉዳት ያስከትላል ፡፡ እጆች እና እግሮች ከልብ በጣም የራቁ የአካል ክፍሎች በመሆናቸው በመጀመሪያ ለዚህ ጉዳት ይዳረጋሉ ፡፡

የስኳር በሽታ ሕክምና ካልተደረገለት ወደ ብዙ ከባድ ችግሮች የሚያመራ ሥር የሚሰድ በሽታ ነው ፡፡ በምርመራው ቀደም ብሎ ህመሙ መኖሩን በመለየት እና በመቆጣጠር ህመሙ ስር ሳይሰድ እና ሌሎች አካላትን ሳይጎዳ በመቆጣጠር የተሻለ ጤና እንዲኖርዎ ማድረግ ይቻላል። ከላይ ከተጠቀሱ ምልክቶች ካስተዋሉ የስኳር ህመም ምርመራ ቢያደርጉ ይመከራል።
ሌሎች ጥያቄዎች ካለዎ ወይም ለማማከር 👉 https://t.me/doctortemesgen 👈 በዚህ ሊያገኙኝ ይችላሉ።
አመሰግናለሁ።

MD, Lecturer, UX & UI Developer, Consultant SMM, and Blogger.

Click to comment

More in ህክምና

To Top